Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዘመናዊ የፎረንሲክ ሰነድ ማጣሪያ ላቦራቶሪ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዘመናዊ የፎረንሲክ ሰነድ ማጣሪያ ላቦራቶሪ ስራ ጀመረ።

የፎረንሲክ ላቦራቶሪው የተገኘው ዓለም ዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት እና የጀርመን መንግስት ለኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ባደረጉት ድጋፍ ነው።

ላቦራቶሪው የተጭበረበሩ የጉዞ ሰነዶች፣ ፓስፖርት፣ ቪዛና ሌሎችንም ዶክመንቶች በቀላሉ መለየት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሙጂብ ጀማል ከዚህ በፊት የጉዞ ሰነዶች የሚረጋገጡት በአይን በማየት ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ “ላቦራቶሪው በየዘመኑ እየተለዋወጠ የመጣውን የወንጀለኞችን እንቅስቃሴ ለመግታት ያግዛል” ብለዋል።

ዘመናዊ የጉዞ ሰነድ ማጣሪያው የአሸባሪዎችንና የሕገ ወጦችን እንቅስቃሴ ለመግታት የቁጥጥር አሰራሩ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በድጋፍ የተገኙት የፎረንሲክ ላብራቶሪዎቹ ከ5 እስከ 7 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ሲሆን ሁለቱ በቦሌ ውሮፕላን ማረፊያ ተተክለው ዛሬ ስራ ጀምረዋል።

አንዱ ላቦራቶሪ ደግሞ በዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት ለማሰልጠኛነት መገጠሙን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም ኢ-ፓስፖርት የሚጠቀሙ ዓለም ዓቀፍ ተጓዦችን አጠቃላይ ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዓለም ዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ልኡክ ሃላፊ ማውሪን አቼንግ “የላቦራቶሪ ማሳሪያው መረጃዎችን በማጣራት ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጣር ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.