Fana: At a Speed of Life!

የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ተቋቋመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግንባታው ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ተቋቋመ።

አዲሱ መስሪያ ቤት በሴክተሩ ያለውን ችግር ከመቅረፍና ጉድለቶቹን በአግባቡ ከመለየት ባለፈ እንደ ፕሮጀክቱ ችግር አይነት መፍትሄ ማስቀመጥ ያስችላልም ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም ዘርፉን ወደ ትክክለኛ ቁመና ለመመለስና የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ውልና ስምምነት መሰረት እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሃላፊነት አለበትም ተብሏል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ተቋሙ የዘርፉን ችግሮች መለየትና መቅረፍ ቀዳሚ አላማው መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ባከናወናቸው ስራዎች የትልልቅ ፕሮጀክቶችን አሁናዊ ቁመና በመመልከት የቁጥጥር ስራ መጀመሩንም ነው የተናገሩት።

አያይዘውም ተቋሙ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ የአሰራር ግድፈት ያለባቸውን ህጎች የማሻሻል ስራ ያከናውናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስራዎች ተቋራጭ ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አምሀ ስሜ በበኩላቸው፥ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በግንባታው ዘርፍ የሚነሱ እና የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር ለባለሙያዎች እንደ ጉልበት በመሆን ለውጤታማነት ያበቃቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ውሀ ነክ ግንባታ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንቱ ኢንጅነር ጌታሁን ታገሰ ደግሞ፥ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መቋቋም ለዘርፉ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አንስተዋል።

በዘርፉ የሚታዩትን የእቅድና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ለችግሮቹ ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠትና የኮንትራት አስተዳደር ስርአቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ፍትሀዊ ተወዳደሪነትንና ተፎካካሪነትን እንደሚያረጋግጥም ጠቅሰዋል።

የተቋሙ መመስረትና ወደ ስራ መግባት በንድፍ ስራዎች በኩል የሚታዩትን ተደጋጋሚ ስህተቶችና ለዘርፉ እድገት መሰናክል የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ታምኖበታል።

በሙሀመድ አሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.