የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የአሰራር ለውጥ ሊያደርግ ነው

By Meseret Awoke

June 05, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመጥን መልኩ የአሰራር ለውጥ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በአሰራር ለውጡ አጠቃላይ ይዘት ላይ የሠላም ሚኒስቴርን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ከተውጣጡ አካላትጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል።

የተቋሙ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንደገለጹት፥ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የአሰራር ለውጥ ለማድረግ ዋነኛ ምክንያት ናቸው።

የከፋ የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ መከሰት፣ የበሽታ ወረርሽኞች መስፋፋት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመርና የኢኮኖሚ እድገትን ተከትሎ የከተሞች መስፋፋትን ለአብነት አንስተዋል።

የቴክኖሎጂ እድገት፣ የአገሪቱ የጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጥ እና ተለዋዋጭ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችም ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬዓለም ሽባባው በበኩላቸው፥ የአሰራር ለውጡ ኮሚሽኑን ለዜጎች አኗኗር የሚመጥን ዘመናዊና ትልቅ ተቋም እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የዲጂታል አሰራርን በመከተል የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመጥን ተቋም መሆን እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን በ1966 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፥ እየተገበረ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ከ2005 ጀምሮ እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!