የሀገር ውስጥ ዜና

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በርካታ መምህራን እየሰለጠኑ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

June 05, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የመምህራን አቅም በማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በርካታ መምህራን በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ በሃገር ውስጥና በውጪ እየሰለጠኑ እንደሚገኙ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ “የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ በኢትዮጵያ’’ በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በጋምቤላ ከተማ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።

በኮንፍረንሱ መድረክ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር አታክልት ገብረኪዳን እንደገለጹት፥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከስርዓተ ትምህርት ክለሳ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።

በተለይም የትምህርት አቅርቦትና ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትና ተሳትፎን፣ ጥራትና አግባብነት እንዲሁም ውስጣዊ ብቃትን ለማጎልበት ሰፊ ሰራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከ35 ሺህ በላይ መምህራን የሚገኙ ሲሆን፥ በርካቶች በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ በሃገር ውስጥና በውጭ በመሰልጠን ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲዎችን የሰው ኃይልና የግብዓት አቅም በማጠናከር የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ዶክተር አታክልት ተናግረዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመደበኛና ተከታታይ ትምህርት 7ሺህ 738 ተማሪዎችን መቀበሉን አስታውቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!