Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተለያዩ ሃገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የምታደርገው ተሳትፎ የሚደነቅና ሊቀጥል የሚገባው ተግባር መሆኑን የተለያዩ ሃገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሃገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ማህበር አባላት ዛሬ የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከልን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የሦስት አገሮች ወታደራዊ አታሼዎች እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላም ለማስፈን እያደረገች ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው።

“ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ከኮሪያ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለዓለም የጋራ ሠላም የበኩሏን አስተዋጽኦ አድርጋለች” ያሉ ሲሆን፥ የተመድ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚያበረታታውን የሴቶች ተሳትፎ ኢትዮጵያ በተግባር ማሳየቷንም ገልጸዋል።

ይህንንም ኢትዮጵያ ከሌሎች ተሳታፊ አገሮች ጋር በትብብር መንፈስ ማከናወኗን የገለጹት ወታደራዊ አታሼዎቹ፥ ተሳትፎዋን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሶንዳ ሴንጋ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ለዓለም ሠላም ብዙ መስዋዕትነት የከፈለች አገር ናት።

“በርካታ ሠራዊቷን ለዓለም እንዲሁም ለአፍሪካ ሠላም ስትል ገብራለች” ያሉት ጄኔራሉ፥ ለሠላም በተደረገ ተጋድሎ ኢትዮጵያ ሴት የሠራዊት አባላትን ጭምር አሰልፋለች ብለዋል።
ይህም የተመድ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሴቶች ተሳትፎ 30በመቶ ይሁን ከሚለው የመርህ ውሳኔ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

በኢትዮጵያ የኮንጎ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ሊዊስ ሮላንድ በበኩላቸው፥ “የኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ የረጅም ዓመት ልምድ ያለው ነው” ብለዋል።

በሠላም ማስከበር ተሳትፎዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ አገር መሆኗን የሚበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የመከላከያ የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር እያደረገች ያለው ተሳትፎ ለማሻሻል የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ሥራ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ግሩፕ ካፒቴን አንድሪው ጊልበርትም በተመሳሳይ፥ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ያላትን ተሳትፎ አድንቀው፥ የሃገራቸው ሠራዊት በተመድ የአፍሪካ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር አብሮ መሥራቱን ጠቁመዋል።

ይህ አጋርነቱ እንደሚቀጥልና በሰላም ማስከበር ተልዕኮ አቅም ግንባታ ሥልጠና ረገድ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ውስጥ ተመድ ባለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያ በአራት ሥፍራዎች ተሳታፊ መሆኗን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.