የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያለው የሚዲያ አጠቃቀም ፍትሃዊ ሊሆን እንደሚገባ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያለው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ፍትሃዊ ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች፥ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያለው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ቅሬታን ሲያስነሳ መቆየቱን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ፥ መሰል ቅሬታዎች በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዳይፈጠሩ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነ ምግባር አዋጅ እና የተለያዩ መመሪያዎች ሊከበሩ እንደሚገባም አንስተዋል።
የአፋር ነጻ አውጭ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አሉ አይዳይሽ÷ ፓርቲዎች ያሏቸውን ፖሊሲና ስትራቴጅዎች በግልጽ ማስተዋወቅ እንዲችሉ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ፍትሃዊነት ጥያቄ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል ዶክተር ጌታሁን ካሳም፥ ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ይኖር ዘንድ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር የሚከተልና አድሏዊ ያልሆነ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን ዕውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃም በበኩላቸው፥ ፓርቲዎች በሀገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ ይወዳደራሉ የሚሉ ጉዳዮች ከተለዩ በኋላ ወደ አየር ሰዓት ድልድል ይገባል ብለዋል።
በአወል አበራ