Fana: At a Speed of Life!

መንግስትን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው ሰላማዊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን መንግስትን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ፡፡

ጉባኤው ከመጭው ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በጻፈው ደብዳቤ ለምርጫው ሰላማዊነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሕዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብና መግባባት እንዲሰፍን ለሚነሱ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሸ በመስጠት ለምርጫው ፍትሃዊነትና ሰላማዊነት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ነው የጠየቀው፡፡

ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉና የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ሊሰጣቸው የሚችሉ ግጭቶች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች መከሰታቸውን ያስታወሰው ጉባኤው፥ ይህም ለንጹሃን ህልፈትና መፈናቀል ብሎም ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅና የህዝቡ አብሮነት ተጠናክሮ የሀገሪቱ ዕድገት እንዲፋጠን መንግሥት በዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያለው ጉባኤው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ፡፡

ከህዝቡ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በመነሣት ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ሊነሱ የሚችሉ አለመግባባቶችን ውይይትና ድርድርን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመጠቀም መፍታት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

የፀጥታና ደኀንነት አካላትም ለምርጫዉ ፍትሃዊነትና ሰላማዊነት የተለመደውን የሕዝብ ወገንተኝነት በማስጠበቅ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ወጣቶችና ሴቶችም በገለልተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሳተፍ ልምዱን በማዳበር ወደ ፖለቲካ ስልጣን ለመምጣት የምርጫ ካርድ ብቻ አስፈላጊ መሆኑን ለህብረተሰቡ በማሳወቅ የሃገርና የህዝብ ደህንነት እንዲጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡

በምርጫው ወንበሩን የሚረከበው መንግስትም ለዜጎች እኩልነትና መብት መከበር እንዲሰራ በመጠየቅ፥ ህዝቡም በሀገራዊ ምርጫ የመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን በመወጣት በምርጫው ሊሳተፍ ይገባልም ነው ያለው፡፡

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ እየተካሄደ ያለው ድርድር ኢትዮጵያን በማይጎዳና በውሃ የመጠቀም መብትን ባረጋገጠና የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሃዊ ጥቅም በማይነካ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.