የሀገር ውስጥ ዜና

በመቐለ ከተማ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ተጀመረ

By Meseret Awoke

June 07, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በመቐለ ከተማ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማሰተማር ሥራ ዛሬ መጀመራቸውን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ወይዘሪት ገነት መብራቱ እንዳሉት፥ የመማር ማሰተማሩ ሥራው የተጀመረው በከተማ በሚገኙ 32 የመንግስት እና ከ30 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች ነው።

በትምህርት ቤቶቹ ዛሬ የመማር ማስተማር ሥራው የተጀመረው ቀደም ሲል ከመምህራን፣ ወላጆችና በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት አመራት አካላት ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሪት ገነት የገለጹ ሲሆን፥ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የማስተካከልና በቁሳቁሶች የማሟላት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በመቐለ በሚገኙ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውስጥ መደበኛ ትምህርቱ ሲጀመር ሁሉም መምህራን የተገኙ ሲሆን፥ ተማሪዎችም እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር አስቴር ይትባረክ በበኩላቸው፥ እንደ መቐለው ሁሉ በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች መደበኛ ትምህርት ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን በተካሄዱ የተለያዩ መድረኮች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ሂደቱን ለማሳካት ከመምህራን ብዙ እንደሚጠበቅ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!