የሀገር ውስጥ ዜና

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ77 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

By Tibebu Kebede

June 07, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ77 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

የልማት ስራዎቹ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እና አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴን ጨምሮ የከተማ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች በተገኙበት ተመርቀዋል።

በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ጎዳና ተዳዳሪዎች መደገፊያ ማዕከል እና በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል የማስፋፊያ ባለ አራት ወለል ህንጻ እንዲሁም የአቃቂ ቃሊቲ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሁለገብ የሥልጠና ማዕከል እንደሚገኙበት ተገልጿል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፥ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የማሰልጠኛ ተቋማት የመሠረተ ልማታቸው የተሟላ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድ በበኩላቸው፥ በበጀት ዓመቱ በክፍለ ከተማው ከ189 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለታቸውን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!