Fana: At a Speed of Life!

የታፈረችና ጠንካራ ኢትዮጵያ  አሸናፊ እንድትሆን ነው የምንሰራው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንዲጠናቀቅ መንግስት በትኩረት እየሰራ  መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ በእንጅባራ ከተማ ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በወቅቱም አቶ ደመቀ ዜጎች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ደመቀ ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው እንደሚሳተፍ ተወዳዳሪ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደመንግስትም ድርብ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።

በመድረኩ የዞኑ ተወካዮች የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ

የቀረቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን አንስተዋል።

“ዛሬ በዚህ መድረክ ተገናኝቶ ቃል ገብቶ ለመሄድና ለምርጫ ቅስቀሳ ሳይሆን በተገቢው መንገድ የህዝብን ሃሳብ ለመስማት ነው” ብለዋል።

በዚህ ምርጫም “አንዱን አጉልቶ ሌላውን አኮስሶ፤ አንዱን አድምቆ ሌላውን ለማደብዘዝ ሳይሆን የታፈረችና ጠንካራ ኢትዮጵያን አሸናፊ እንድትሆን ነው የምንሰራው” ብለዋል።

አቶ ደመቀ ከህግ ማስከበር ዘመቻ እና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ስላለው ሁኔታ፣ የውጭ ሃገራትን ጫና በተመለከተ ፣የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና የ2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት እና ከሱዳን ጋር ስላለው  የድንበር ጉዳይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አኳያም መንግስት በሽግግር ጊዜ የሚያጋጥም ብቻ ነው ብሎ የሚያልፈው ሳይሆን ከውጭ ሆኖ በፋይናንስ ከሚደግፈው አንስቶ እስከ በሃገር ውስጥ ተቀምጦ የዜጎችን ህይወት እስከሚነጥቀው ባንዳ ድረስ ለማስቆም በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሚወዳደሩ እጩዎቹን የማስተዋወቅ እና የማኒፌስቶ ማስተዋወቅ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የብልጽግና ፓርቲ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ባለፉት 3 ዓመታት የተፈጠረው ሃገራዊ ለውጥ ዛሬ በርካታ ፓርቲዎች በምርጫ ፉክክር እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ አስችሏል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ለመወዳደር በፓርቲያቸው በኩል እጩ ሆነው ከቀረቡት መካከል ይገኙበታል።

በምስክር ስናፍቅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.