የሀገር ውስጥ ዜና

ከቀሬጎሃ (ጐሃፅዮን) እስከ ደጀን ያለው የዓባይ በረሃ በደን ሊሸፈን ነው

By Meseret Awoke

June 09, 2021

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቲዩት የባዮ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ አቶ አዱኛው አድማስ ከቀሬ ጎሃ (ጐሐፅዮን) ወረጃርሶ ወረዳ እስከ ደጀን ያለው የዓባይ በረሃ በደን ሊሸፈን መሆኑን አስታውቀዋል።

ተመራማሪው ከሰሜን ሸዋ ዞን ከቀሬ ጎሃ (ጐሐፅዮን) ወረጃርሶ ወረዳ እስከ አማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ደጀን ወረዳ የሚዘልቀው የዓባይ በረሃ በደን ለመሸፈን የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቲዩት፣ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የተቀናጀ ሥራ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በቆላ የቀርከሃ ተክል የመሸፈንና አረንጓዴ አሻራ የማኖር ሥራ ተጀምሯልም ነው የተባለው።

ከቀሬጎሃ (ጐሐፅዮን) እስከ ደጀን ያለው የዓባይ በረሃ ከፍተኛ የሆነ ማዕድንና አሸዋ መገኛ በመሆኑ እንዲሁም ማዕድኖችን የማውጣት ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም መልሶ የማልማት ሥራ ባለመከናወኑ የመሬት መራቆትና አፈር መሸርሸር እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአካባቢው ቀደም ሲል የነበረውን ደን በመጨፍጨፍ አርሶ አደሮች ለከሰል እና ለሌላ አማራጭ ስለተጠቀሙበት አካባቢው ለመሬት መራቆት መጋለጡንና ለኑሮ አስቸጋሪ መልክዓ ምድር እየሆነ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅትም የቀረው የእንጨት ዝርያ ለከሰል ኃይል ምንጭ ሲባል እየተጨፈጨፈ እና አፈር እየተሸረሸረ በቀጥታ ወደ ዓባይ ወንዝ እየገባ ነውም ተብሏል።

በመሆኑም አካባቢውንም ሆነ የዓባይን ወንዝ ከችግር ለመታደግ በረሃማውን አካባቢ በቀርከሃ ደን የመሸፈን ልዩ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!