የሥራ ዕድል ፈጠራን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር በሁለት ወገን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተገለጸ

By Meseret Awoke

June 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የሥራ ዕድል ፈጠራን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር በሁለት ወገን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት መንገድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነን ገለጹ፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ የ2013 ዓ.ም የ9ወራት አገራዊ አፈፃፀም እና የመረጃ ጥራት ዳሰሳ ውጤት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን በሚመሩት የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

የ2013 የበጀት ዓመት ሃገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅዱ 3 ሚሊየን የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዘጠኝ ወራት ደግሞ 2ነጥብ 55 ሚሊየን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ የተጀመረ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ዕቅዱም በየክልሎቹ የተከፋፈለ እና የተሰጠ ቢሆንም፥ ክልሎች የየራሳቸውን ፀጋ ለይተው ተጨማሪ ዕቅድ ይዘዋልም ነው የተባለው፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት በዘጠኝ ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ 2ነጥብ 8 ሚሊየን የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡

ከነዚህም የግብርና ዘርፉ 29 በመቶ ፣ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 30 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ 41በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መነሻነትም ከምክር ቤቱ በተነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያም ውይይት ተደርጓል፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ብለው ያስቀመጧቸው የወጣቱን የሥራ ባህልና አመለካከት መቅረጽ ሥራ ከመንግስት ባለፈ ወላጆች ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲሁም ወጣቶችም በአካባቢያቸው ያሉ ጸጋዎችን በመለየት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማሕበረሰቡ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር በሁለት ወገን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን መንገድና በተለይም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን የማጠናከር ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!