የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ አፍሪካ ሠላማዊ ሠልፍ ተጠራ

By Meseret Awoke

June 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ ሠላማዊ ሠልፍ መጠራቱን የሠልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ለመደገፍ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ኃይሎችን ለመቃወም እና እስካሁን ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ሀገራትን ለማመስገን ሠላማዊ ሠልፍ መጠራቱን ነው ኮሚቴው ያስታወቀው፡፡

ኮሚቴው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ሰኞ ” ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫና በማድረግ እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመቃወም ሠልፉ ይካሄዳል ብሏል፡፡

በሠልፉ ጣልቃ ገብነትን እንዲያቆሙ ለአሜሪካ እና ለአውሮፖ ህብረት መልዕክት የሚተላለፍ ሲሆን፥ የደቡብ አፍሪካ መንግስትና ህዝብ ደግሞ እስከዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ጎን በመቆም ለሰጡት ድጋፍ ምስጋና እንደሚያቀርቡም አስታውቋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የወጣውን የኮቪድ19 መመሪያ ለመጠበቅም በሠልፉ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ከሃይማኖት ተቋማት ከማህበረሰቡ እና ከመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ የኮሚቴ አባላት ኢትዮጵያውያን በሠልፉ እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!