Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ እና አሜሪካ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ያተኮረ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋሽንግተን በኢትዮጵያ እና አሜሪካ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ያተኮረ ፎረም ተካሄደ፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተካሄደው ፎረም የአሜሪካና ኢትዮጵያ ቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚል መሪ ቃል በበይነ መረብ ነው የተካሄደው፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ለአሜሪካ ኩባንያዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የተካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና በመንግስት የተደረጉ ማሻሻያዎችን እንዲሁም የ10 አመቱን የልማት እቅድ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ግብርና፣ የማምረቻው ዘርፍ፣ የቱሪዝም ልማት፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ፣ የሃይል ዘርፍ እና የማዕድን ዘርፎች ለአሜሪካ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በማብራሪያቸው መንግስት የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አያይዘውም አሁን ላይ መንግስት ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍን እና ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አብራርተዋል፡፡

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጅ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ፈተናዎች ወጥታ የአሜሪካ ቁልፍ የኢኮኖሚና የደህንነት አጋር መሆኗን እንደምትቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.