Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እንዲያረጋግጥ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ሊጠናከር ይገባል- ዶ/ር አረጋዊ በርሄ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እንዲያረጋግጥ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ጥሪ አቀረቡ፡፡
9ኛውን ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ ምክንያት በማድረግ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከተራሮችና ሀይቆች የሚፈሱ የአባይ ገባር ወንዞች አመቱን ሙሉ የውሃ ፍሰታቸው እንዳይዛባ ችግኞችን በመትከልና በመከባከብ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ እንደ ሀገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብን ከደለል በመታደግ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ ለማስቻል ሀገራዊ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
”ቀሪውን 20 በመቶ ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውን ዛሬም እንደትናንቱ በህብረትና በአንድነት ለህዳሴው ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍና አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ” አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገለጫ በመሆኑ የግድቡን ህልውና ለማስጠበቅ እንደ ሀገር የተጀመሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በህዳሴው ግድብና በዓለም አቀፍ የውሃ ህጎች ላይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀን ሲመክር የቆየው ሀገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤም በዛሬው እለት ተጠናቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.