የአዊ ባሕል ማዕከልን በአዲስ አበባ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1ሺህ 700 ካሬ ሜትር ላይ ለሚያርፈው የአዊ ባሕል ማዕከል በአዲስ አበባ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጧል።
ለቢሮ እና ለተለያዩ ሥራዎች አገልግሎት የሚሰጥ ዋና መስሪያ ቤቱን ለመገንባት የፌዴራል ባለስጣናትና ሚኒስትሮች እንዲሁም የአካባቢው ተወላጆች በተገኙበት ነው የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ህንጻው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የባሕልና ወግ እሴቶችን ጠብቆ ለመሻገር እንዲሁም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አንድነትን አጠናክሮ ለመቀጠል ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ የአዊ ባሕል ማዕከል ግንባታ በቀጣይ ከሚገነባው የአማራ ባሕል ማዕከል ጋር ተዳምሮ ለከተማዋ ውበትና ልዩ ድምቀት ነው ብለዋል፡፡
ህንጻው የተለያዩ አገልግቶችን እንዲሰጥ ታስቦ የሚገነባ ነው ያሉት የአዊ ልማት ማኅበር ቦርድ አባልና የአዲስ አበባ ቅርጫፍ አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው ህንጻው ከ15 እሰከ 20 የሚደርሱ ወለሎችን የሚይዝ ነው፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳይ ዘሪሁን ህንጻው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የአዊ ሕዝብን ባሕል፣ ወግና አኗኗር በቅርበት ማየትና መጎብኘት ለማይችሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች በቅርበት እዲያውቁ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የአዊ ልማት ማኅበር በ1999 ዓ.ም እንደተመሰረተ ከአሚኮ የያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!