የሀገር ውስጥ ዜና

ኢዜማ የምርጫ 2013 የምረጡኝ ዘመቻ ፍፃሜ መርሐ-ግብር አካሄደ

By Tibebu Kebede

June 13, 2021

 

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የምርጫ 2013 የምረጡኝ ዘመቻ ፍፃሜ መርሐ-ግብር በግዮን ሆቴል አካሂዷል።

በመርሐ-ግብሩ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፥ “የድምፅ መስጫው ዕለት የመጨረሻ የልፋታችንን ውጤት የምናይበት በመሆኑ በጉጉት የምንጠብቀው ነው” ብለዋል።

ላለፉት 4 ወራት በነበረው የምርጫ ዘመቻ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የፓርቲው አመራሮች እና አባላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው፣ “በተለያየ ደረጃ የምንገኝ የኢዜማ ኃላፊዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎች በሙሉ ደማቅ አቀባበል ያደረጋችሁልን፤ በይበልጥ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እና ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ምን ያህል ስር የሰደደ ድጋፍ እንዳለው በግልጽ ላሳያችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋናችን ይድረሳችሁ” ብለዋል።

“ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ዕምነቶች ተከታይ ዜጎች ያሉባት፣ ባለብዙ ባህል፣ ታሪክ እና ቅርስ ባለቤት ሀገር ነች፤ ሁሉም ዕምነቶች፣ ባህሎች እና ቅርሶች እኩል ኢትዮጵያዊ ናቸው” ብለዋል የኢዜማ መሪው።

በኢዜማ ዕምነት ይህ ብዝኃነት የጥንካሬ፣ የውበት እና የጋራ ዕድገት መነሻችን እንጂ የመከፋፈያ እና የድክመት ምንጭ እና የግጭት መፈልፈያ መሆን እንደሌለበትም ገልፀዋል።

በምረጡኝ ዘመቻ የፍፃሜ መርሐግብሩ ላይ ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች እና አባላት ተሳትፈዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!