Fana: At a Speed of Life!

በ550 ሚሊየን ብር የተገነባው የግብርና ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካ በይፋ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በ550 ሚሊየን ብር ካፒታል የተገነባውን ማንቶ የግብርና ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፋብሪካን በይፋ ስራ አስጀምረዋል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ወቅት ፋብሪካው በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ለተሰማሩ 250 አርሶ አደሮች የግብርና መገልገያ እቃዎች በስጦታ አበርክቷል።

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን እና ሜካናይዝድ ማድረግ ይገባል።

እንደ ማንቶ ያሉ የግብርና ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካዎችን በማገዝ ዘመናዊ ግብርና እንዲስፋፋ ማድረግ ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ፋብሪካው ለሚያከናውናቸው ስራዎች የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪው በከተማዋ በግብርና ስራ ለተሰማሩ 250 አርሶ አደሮች ላደረገው ድጋፍ አመስግነው መሰል በጎ ተግባራት ለሌሎችም ኢንዱስትሪዎች አርአያ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የማንቶ የግብርና ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብራር ሙራድ ዘመናዊ ግብርናን በማሳደግ አርሶ አደሮች ጉልበታቸውን ቆጥበው ምርታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የግብርና መሳሪያዎችን ማምረት እንደሚያስችል ገልጸዋል ።

ፋብሪካው ከ450 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.