ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ክልል ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ክልል ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት ከ2 ሺህ የሚበልጡ ተወካዮች ተሳታፊዎች ናቸው።
ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የወጣት ተወካዮች በውይይት መድረኩ ላይ ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊዎቹ በክልል መደራጀት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።
እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የመንገድ ችግር እንዳለ፤ የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የጤና ባለሙያዎች እና የመድሃኒት እጥረት እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባልተዳረሰባቸው ዞኖችም ተቋማቱ እንዲገነቡ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን ወዳልሄዱባቸው ዞኖች ሄደው ከህዝብ ጋር ለምን አልተወያዩም የሚል ጥያቄም ቀርቧል።
በሀገሪቱ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መሰራት አለበት ባሉት ጉዳይ ላይም ሃሳብ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፥ ከሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተነጋግሮ መፍትሄ የማበጀት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ከመሰረተ ልማት ጋር እና ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዘው ለቀረቡ ጥያቄዎችም አንድ የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ታች ድረስ ዘልቆ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራም ነው የገለፁት።
በክልል ከመደራጀት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም፥ በክልል ከመደራጀት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ መድረክ ላይ መልስ መስጠት እንደማይቻል አስረድተዋል።
ነገር ግን የሀገርን አንድነት እና የዜጎችን አብሮነት በማይጎዳ መልኩ በክልል ከመደራጀት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሂደት መፍትሄ እያገኙ ይሄዳሉም ነው ያሉት።
በአልአዛር ታደለ