Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅንና ደንብ መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባኤው የውጪ ድግግሞሽን ኦዲትን ለማስቀረት የወጣውን ረቂቅ አዋጅና የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ ደንብ መርምሮ አፅድቋል፡፡

ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳቦቹን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  አቶ መሐመድ ዮሱፍ÷ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁንና ረቂቅ ደንቡን ለዝርዝር እይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ከመራው በኋላ በተለያዩ ቀናት ከአስረጂዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ በቂ ግብዓት እንደተገኘ  አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ዮሱፍ ÷የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወጪ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅ በፌዴራል መንግሥት የሚደረገውን የበጀት ድጋፍና ድጎማ በተመለከተ በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተሮች የሚደረገውን  የኦዲት ድግግሞሽን  እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አያይዘውም አዋጁ በኦዲት መስሪያ ቤቶች ላይ የሚኖረውን የሥራ ጫና፣ የጊዜና የሰው ኃይል ብክነት እንደሚያስቀርም ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1251/2013 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

በሌላ በኩል  አቶ መሐመድ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ደንብ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ማብራሪያም ደንቡ የኦዲት ሥርዓቱን በማጠናከር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሚገባ ለመምራትና ለማስተዳደር መረጃ እንዲያገኝ የሚረዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የልማት ድርጅቶችንና ፕሮጀክቶችን የገንዘብ አስተዳደር፣ የሂሳብ አያያዝ፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የወጪ አፈቃቀድና የንብረት አያያዝ ሕጉን ተከትለው እንዲፈፀሙ ያደርጋቸዋልም  ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ የቀረውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ ረቂቅ ደንቡ ደንብ ቁጥር 11/2013 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.