Fana: At a Speed of Life!

ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ-ዝግጅት መጨረሳቸውን የአማራ እና የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ-ዝግጅት መጨረሳቸውን የአማራ እና የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽኞች አስታወቁ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ ÷6ኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ ፖሊስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በሰጡት መግለጫ÷ ምርጫ በአንድ ሃገር የህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱንና ልአላዊነቱን በተግባር የሚረጋገጥበት በመሆኑ  ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ፖሊስ ከፍተኛ ሀላፊነት አለበት ብለዋል።

በመሆኑም 6ኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ዝግጅቱን አጠናቋል ሲሉ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ በሚከውናቸው ተግባራት ላይ በቂ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን÷ ለዚህም በየደረጃው የሚገኝ ሁሉም የፖሊስ ሃይል ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል መግባባት ላይ ተደርሶ ኮማንድ ፖስትም ተቋቁሟል ሲሉ ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

 

የፖሊስ ኮሚሽኑ ከፍተኛ መኮንኖች በሁሉም ዞኖች ሆነው ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን÷ በቅድመ ምርጫው ሂደት እስካሁን ድረስ ከጥቃቅን ጉዳዮች ውጭ የጎላ ችግር አለመከሰቱን ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።

በምርጫው ወቅት እና ከምርጫ በኋላም ቢሆን ህዝቡ ያላንዳች የፀጥታ ስጋት የሚፈልገውን በመምረጥ የተለመደ ተግባሩን እንዲያከናውን ለማስቻልና ስጋቶችን ለመቅረፍ ከህዝቡ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት ።

በመጨረሻም ኮሚሽነሩ ለምናደርገው ማንኛውም የፀጥታ ስራ ህዝቡ ከጎናችን እንዲሆን ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተመሣሣይ ዜና ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ-ዝግጅት መጨረሱን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጨ ቦርድ ባዘጋጀው የሙያ ስነ-ምግባር መመሪያ መሰረት በየደረጃው ለሚገኙ የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላትን በማሰልጠን ገለልተኛ ሆኖ መስራት የሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ከክልሉ የምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በቅንጅት በመስራት የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እንዳይስተጓጎል እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አሊ ዲኔ ለፋና ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሕዝብ አስቀድሞም ቢሆን ሰላሙን በመጠበቅ የሚታወቅ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ሕብረተሰቡ በምርጫ ቀንና ከምርጫ በኋላም ከፖሊስ ጎን በመቆም ሰላሙን እንዲያስጠብቅ ጥሪ ማቅረባቸውን በስፍራው የሚገኘው ባልደረባችን ርስቴ ጸጋዬ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.