Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሎጂስቲክ ፓስፖርት ተቋም አባል ሆነች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የዕቃዎች አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር አማካኝነት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የሎጂስቲክ ፓስፖርት ተቋም አባል ሆናለች።

ዓለምአቀፉ የሎጂስቲክ ፓስፖርት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ የተመሠረተ ተቋም ነው።

ተቋሙ ዓለም አቀፍ ብሔራዊ የንግድ ተቋማትን ከሎጂስቲክ የአሠራር ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር እንዲሁም ለታዳጊ ገበያዎች የተለያዩ ዕድሎችን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

ዱባይን ዋነኛ የመገናኛ ማዕከል በማድረግም አፍሪካ፣ እስያና ላቲን አሜሪካን በማገናኘት ቀልጣፋ የሎጂስቲክ መረብ ለመፍጠር ትኩረት ማድረጓን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ውብሸት፥ ኢትዮጵያ በማኅበሩ በኩል የተቋሙ አባል ሆናለች ብለዋል።

አባል በመሆኗም በዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘትና የተሻለ የአቅርቦት ሰንሰለት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ የእቃ ጭነት ማስተላለፍ ጊዜውን በማሳጠርና ዘመናዊ የክትትል ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ አባልነቷ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

ከላቲን አሜሪካና ከእስያ ጋር የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከርና ኢትዮጵያም ከሁለቱ አህጉራት ግዙፍ የጋራ የገበያ ድርሻ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታልም ብለዋል።

የኢትዮጵያን የውጭ ምርቶች በዓለም ገበያ በቀላሉ ለማስተዋወቅና በውጭ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በዘርፉ የቴክኖሎጂና የክህሎት ልውውጥ በማድረግም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች ያሉ ሲሆን፥ ተቋሙ እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 ሃገራትን በአባልነት አቅፏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.