በደቡብና ሲዳማ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት በአብዛኛው ቦታዎች ላይ ደርሷል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርጫ ቁሳቁሶችን ስርጭት በአብዛኛው ቦታዎች ላይ መድረሱን የደቡብ ክልልና የሲዳማ ክልል ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት አስታወቁ፡፡
የምርጫ ቁሳቁሶችን የማቅረቡ ስራ ከትላንት ጀምሮ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ በየአንዳንዱ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ስራ በመከናወኑ ወደየ ምርጫ ጣቢያዎቹ እየተሰራጩ መሆኑንም የፅ/ቤቱ ሀላፊ አቶ ፍሬው በቀለ ተናግረዋል።
በአብዛኛው አካባቢዎች የማድረስ ስራዎችን የተከናወኑ እና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላይም የተለያዩ መጓጓዣዎችን በመጠቀም የማድረስ ስራው እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
የማጓጓዝ ስራውም በተለያዩ ተሽከርካሪዎች በመታገዝና አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎች ላይ በእንስሳትና በጀልባዎች ለማድረስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ የአየር ትራንስፖርትን መጠቀምም ማጓጓዝ እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬው እለት የተቀሩ አካባቢዎች የማዳረሱ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን እስከ ነገ ጠዋት ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሁለቱም ክልሎች አንድ መቶ ሰላሳ ሁለት የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን፣ በሲዳማ ክልል አስራ ጠዘኝ የምርጫ ክልሎች ያሉበትና በዚያም 2 ሺ ሁለት መቶ ሰላሳ አራት ምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ በመግለፅ፣ ደቡብን በተመለከተ አንድ መቶ አስራ ሶስት መደበኛና ልዩ የምርጫ ክልሎች ያሉበትና ስምንት ሺ አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ ብለዋል ።
ደቡብ ክልልን በተመለከተ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የተወሰነ የህትመት ችግር ያለባቸውና ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ ምዝገባ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተለይተዋል።
ባጠቃላይ በሀያ አምስት(25) የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አንድ ሺ ስድስት መቶ ሰማንያ ሁለት የምርጫ ጣቢያ ላይ ምርጫ የማይካድባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
በሁለቱም ክልሎች ሀምሳ ሶስት ሺ የሚሆን የሰው ሀይል ምርጫን ለማስፈፀም ተሰማርቶ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በሲዳማ ክልል አስራ ሁለት የፖለቲካ ፖርቲዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ሀያ ሶስት የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚገኙ ሲሆን እጩዎቻቸውን አቅርበው መራጩን ህዝብ ድምፅ እንዲሰጣቸው እየተጠባበቁ ይገኛሉ ብለዋል።
በብርሃኑ በጋሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!