የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፖሊሳዊ የደንብ ልብስ እና ዓርማ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2013(ኤፍ ቢ ሲ) – በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ የተጀመረው የለውጥ ስራ አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፖሊሳዊ የደንብ ልብስ እና ዓርማ የማብሰሪያ መርሀ-ግብር አካሂዷል::
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የፖሊስ ኃይል በደንብ ልብሱ በሰነቀው አላማ አንድነትንና ህዝባዊነትን በብቃት ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል።
ፖሊስነት አምኖ ለተቀበሉት ታላቅ አላማ ራስን ለህዝብ ደህንነት አሳፎ መስጠትት ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ ::
ባለፉት 3 ዓመታት ጸረ-ሰላም ሐይሎች አዲስ አበባን የነውጥና የብጥብጥ ማእከል ለማድረግ ቢያስቡም የከተማዋ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ እና ብሔራዊ የደህንነት አካላት በጋራ በመስራታቸው ሴራው ሳይሳካ ቀርቷል ነው ያሉት።
ህብረተሰቡም ጸረ ሰላም ሃይሎቹን በመታገል ዋና ተዋናይ እንደነበር አመልክተው፤” የተጀመረው የፖሊስ ሠራዊት የለውጥ ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ተባባሪነታችሁ አይለየን” ብለዋል።
ይህም አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ሙያዊ የፖሊስን የህዝብ ወገንተኝነት ለማረጋገጥ ብሎም ፖሊሳዊ አገልግሎት ሕግንና ሕግን ብቻ መሰረት አድርጎ አንዲሰጥ ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“የደንብ ልብስን ከመቀየር ጀምሮ የተገልጋዩን እርካታ አላማ ያደረገ የለውጥ ጉዟችን ይቀጥላል” ያሉት ኮሚሽነር ጌቱ፤ የፖሊስ አደረጃጀት የከተማውን አደረጃጀት በተከተለ መልኩ እንዲዋቀር ስራዎች እየተሰሩ ነመሆኑንም ገልጸዋል።
በከፍተኛ ወጪ በተዘረጋ ዘመናዊ ቴክኖሎጂም የፖሊስ የግንኙነት መንገዶች መገንባቱን ተናግረዋል።
ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ህገወጥ ተግባራትን በማጋለጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል::