በምስራቅ ሸዋ ዞን በሚገኙ አብዛኞቹ ወረዳዎች የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ጣቢያዎች ደርሷል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 13 ፣ 2013 ፣ (ኤፍ ቢ ሲ) በነገው ዕለት ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን የምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ደበሌ ወርቁ እደገለጹት÷ እስካሁን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ተከናውኗል፡፡
ቀሪውን የቁሳቁስ ስርጭት ዛሬ እስከ 6 ሰዓት ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው÷መንግስት የሎጂስቲክ አቅርቦት እገዛ ማድረጉ ለሂደቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
የፀጥታ አካላትም ከፀጥታና ደህንነት ጥበቃ በተጨማሪ በቁሳቁስ ስርጭት ወቅት አስፈላጊውን እጀባ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም በቀጣይ 5 ዓመታት የሚያስተዳድራቸውን ፓርቲ ለመወሰን ድምፃቸውን በነቂስ ወጥተው አንደሚሰጡ አረጋግጠዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን 11 የምርጫ ክልሎችና 1ሺህ 540 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሱሆን ÷ ከ 1 ሚሊየን 18 ሺህ በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ