Fana: At a Speed of Life!

ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የሐሰት ዘገባዎች እንዳይታለል መጠንቀቅ አለበት-የዘርፉ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ ሐሰተኛ ዘገባዎች እንዳይታለል ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የመረጃ አጣሪ ባለሙያው አቶ ባህሩ ደምሴ አሳሰቡ።

አቶ ባህሩ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት የተሳሳቱ መረጃዎችን እያስተላለፉ ነው ብለዋል።

በተለይም ሰሞኑን ምርጫውን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በማሰራጨት ኅብረተሰቡን ለማደናገር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ የሐሰት መረጃዎች ላይ መጠመዳቸውን ነው የጠቆሙት።

እነዚህ አካላት ድብቅ አጀንዳቸውን ከማሳካት በዘለለ ባሏቸው የዩቲዩብ ጣቢያዎች ገቢ የመሰብሰብ ሥራ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ስለዚህም ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን በጥንቃቄ ለመመለከትና ትክክለኛነታቸውን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመረጃዎችን ትክክለኝነት ከመገናኛ ብዙሃንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ይፋዊ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃንም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን አስቀድመው በመለየትና ትክክለኛ መሆናቸውን በማጣራት ለሕዝቡ ሊያሳውቁ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃ የሚያሰራጩ አካላትንም የማጋለጥ ሥራ ከመገናኛ ብዙሃን እንደሚጠበቅ አቶ ባህሩ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ሳምሶን መኮንን ምርጫውን ተከትሎ የሃሰተኛ መረጃዎች ተጠባቂ ናቸው ይላሉ።

በተለይም በኢትዮጵያ በአብዛኛው የተሳሳተ መረጃ የሚሰራጩት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ፌስቡክ እና ዩቲዩብ መሆናቸውንም ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህ አይነቱ ችግር ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡ የሚሰራጩትን መረጃዎች ትክክለኝነት ማረጋገጥ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በተለይም የመገናኛ ብዙሃን በምርጫው ዕለትና ከምርጫው በኋላ የመረጃዎችን ትክክለኝነት አጣርተው በመዘገብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው ያስገነዘቡት።

የመገናኛ ብዙሃንና ተግባቦት ከፍተኛ አማካሪ ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱም የመረጃ መዛባትና የተሳሳቱ መረጃዎች ሥርጭት በምርጫ ወቅት ያጋጥማሉ ብለዋል።

የሀሰተኛ መረጃና የመረጃ መዛባት የስርጭት እድል የሚኖረው ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት ተፅዕኖ ውስጥ ሲገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለሆነም የመረጃ ምንጮች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፤ ጋዜጠኞች ደግሞ ትክክለኛ መረጃዎችን በማቀበል ኅብረተሰቡን ከብዥታ ማውጣት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.