ስፓርት

በትግራይ ክልል ሲካሄድ የቆየው የብቃት ምዝና አትሌቲክስ ውድድር ተጠናቀቀ

By Meseret Demissu

June 22, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይ ክልል ለአንድ ሳምንት ያህል ሲካሄድ የቆየው የብቃት ምዘና የአትሌቲክስ ውድድር ተጠናቀቀ።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አትሌትክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ማሞ ÷በክልሉ በነበረው ችግር ለሰባት ወራት ያህል ተቋርጦ የቆየውን የአትሌቲክስ ውድድር ማስቀጠል ተችሏል።

በዚህም በትግራይ አለም አቀፍ ስታድዮም ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ሲካሄድ በቆየው ውድድር ከእንደርታ እና ህንጣሎ ዋጀራት ወረዳዎች እና መቀሌ ከሚገኙ አምስት ክፍለ ከተሞች የተመረጡ 261 አትሌቶች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

አትሌቶቹ በ100፣ 800፣ 1ሺህ500 ፣ 3ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የብቃት ምዘና ውድድር አካሄደዋል ብለዋል።

የአሎሎ፣ ዴስክና ጦር ውርወራ የውድድሩ አካል መሆናቸውን  አመላክተዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች፣ ኮኮብ አሰልጣኞች፣ ተሳታፊ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች የገንዘብ ፣ዋንጫና ሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ በ100 ሜትር አንደኛ በመውጣት የዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው አትሌት ፋና አጽበሀ በሰጠችው አስተያየት÷ ስፖርት የተረበሸ አእምሮ የማከም ብቃት ያለው በመሆኑ ውድድሩ በመዘጋጀቱ ተደስቻለሁ ብላለች።

በሌላ በኩል  በቶክዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በመወከል ከሚወዳደሩ መካከል ክልሉ ሰባት አትሌቶችን ማስመረጡን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።

ከተመረጡትም መካከል ለተሰንበት ግደይ እና ጽጌ ገብረሰማ በ10ሺህ ፣ጎድፍ ጸጋይ በአምስት ሺህ ሜትር እንዲሁም ከወንድ አትሌቶች ደግሞ በሪሁ አረጋዊና ሀጎስ ገብረህይወት በ10ሺህ ሜትር እንደሚሳተፉ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!