በ600 ቢሊየን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ኮርፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ተሾመለት
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በ600 ቢሊየን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ተሹሞለታል፡፡
አቶ ሙሉአለም ጌታሁን የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የዕዳ ጫና በማቃለል ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ የሚያግዝ አዲስ ተቋም መሆኑ ይነሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ በማቃለል በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ለማስወገድ የሚያግዝ የመንግስት ድርጅት ነውም ተብሎለታል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የተዘፈቁ 7 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ማለትም የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የኤልክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን)፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ስኳር ድርጅት እዳና ሀብት እንደሚያስተዳደር ታወቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የንግድ ተቋም ቁመና የሚይዝ በመሆኑ ዕዳው በመንግስት በጀት ላይ ጫና እንደማይፈጥር ታምኖበታል፡፡
በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑ በንግድ ተቋምነት መመስረት ብቃት ያላቸውን አመራሮችና ባለሞያዎችን በመያዝ በገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች እንደሚሰማራም ታሳቢ ተደርጓል፡፡
መንግስት የልማት ድርጅቶቹ ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁና በሀገር እድገትና ልማት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ሁል አቀፍ የማሻሻያ አጀንዳዎችን ቀርጾ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷልም ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑ መመስረት የልማት ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም የነበረውን የብድር አስተዳደራቸውን የሚያዘምንና በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑ ታወቋል፡፡
የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በጥር ወር 2013 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም የተወሰነ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፥ ተጠሪነቱም ለገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!