Fana: At a Speed of Life!

የምርጫ ውጤትን አስመልክቶ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል – የአዲስ አበባ ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርጫ ውጤትን አስመልክቶ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ÷ በአዲስ አበባ የድምፅ ቆጠራው መጠናቀቁን ተከትሎ ድምፅ የተሰጠባቸው ወረቀቶችና ተያያዥ ቁሳቁሶች በሰላም ወደ ምርጫ ክልል ፅህፈት ቤቶች መጓጓዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ሃይሉ የጋራ እቅድ በማውጣት፣አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላትና ስልጠና በመውሰድ እንዲሁም ልዩ ልዩ የክትትል እና የቁጥጥር አደረጃጀቶችን በመፍጠር ወደ ተግባር ገብቶ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስ፣ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ያከናወኑት ተግባር ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የድህረ ምርጫው ምዕራፍም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ማህበረሰቡ እንዲሁም የሚዲያ አካላት የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜጎች በነፃነት ካለስጋት ድምፃቸውን መስጠታቸው የጋራ ውጤት መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጌቱ ÷ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት በመወጣት አኩሪ ተግባር ለፈፀሙት ለመላው የፀጥታ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የምርጫ ውጤትን አስመልክቶ የተዛባ መረጃ መሰራጨቱ በምርጫው ሰላማዊ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያሳድር ስለሚችል የምርጫ ቦርድ የሚያሳውቀውን ይፋዊ ውጤት በመጠበቅ ህጋዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና በዚህ ዙሪያ ኮሚሽኑ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በምርጫ ህጉ መሰረት እርምጃ እንደሚወስድ ነው ያሳሰቡት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.