Fana: At a Speed of Life!

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስራ እድል ፈጠራን ማበረታታትና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማገዝ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ተፈራርሟል።

ስምምነቱን በሃገር ውስጥ የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶችን በተሻለ ጥራት ለማምረትና የዘርፉን የስራ እድል ፈጠራ ለማስፋት ያለመ ነው ተብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ስምምነቱ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል እንዲሁም የሃገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለውጭ ገበያ ጭምር እንዲቀርቡ የማመቻቸት ስራዎችንም ያካትታል ብለዋል።

በተጨማሪም የትምህርት ቤት ቦርሳና ጫማ በስፋት በማምረት ለተማሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በነጻ ለማቅረብ እየተሰራ ያለውን ስራ መደገፍም በስምምነቱ መካተቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ኮንዴ ፥ ፋውንዴሽኑ በስራ እድል ፈጠራ ወጣቶችን በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልጸው ፥ በፋውንዴሽኑ ስር የሚተገበረው ብሪጅስ የተሰኘው ፕሮግራም ለወጣት አፍሪካውያን የስራ እድል ፈጠራና ስልጠና በማመቻቸት ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

የተፈረመው ስምምነትም ምርትና ምርታማነትን በማስፋት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ በኢትዮጵያ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ከፓርኮቹ ጋር የማስተሳሰር እድል ያመቻቻል።

ፋውንዴሽኑ ከሚሰጣቸው የተግባር ስልጠና በኋላ ስራ የሚፈጥሩበት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ድጋፉ ሚኒስቴሩ በመለመላቸውና ብቃታቸውን ባመነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሰማሩ ወጣቶች ሲሆን፥ በአስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.