Fana: At a Speed of Life!

የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንትነር ተርሚናል በይፋ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንቴነር ተርሚናል በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡

የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂ፣ የኢፌዴሪ ከፍተኛ ልዑካን እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ስራውን ጀምሯል።

በዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ በሶማሊላንድ 30 በመቶ እና በኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻው የተያዘው የበርበራ ተርሚናል ኮሪደር የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቴነሮችን የሚይዝ ሲሆን፥ በዓመት 1 ሚሊየን ኮንቴነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል።

ወደቡ ዘመናዊ ክሬኖች የተገጠሙለት ሲሆን፥ ከዛሬ ጀምሮ ግዙፍ መርከቦችን በማስተናገድ ለቀጠናው በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ እንደቀየሰችና የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ለማሳደግ ወደቦችን ማልማትና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ የወደቡ መከፈት ለኢኮኖሚው ትልቅ ሚና አለው።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፥ የበርበራ ወደብ የመጀመሪያው ዙር ተርሚናል ስራ መጀመር በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደትን ከፍ እንደሚያደርግና በተለይ በየጊዜው እያደገ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በበርበራ ወደብ ላይ ለሚደረገው ስራ ኢትዮጵያ ትካፈላለች ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ፥ የሶማሊላንድ ልማትና ዕድገት የኢትዮጵያ በተለይ የሶማሊ ክልል እድገት እንደሆነ ጠቁመው፥ የበርበራ ወደብ ለቀጠናው ህዝብ ፋይዳው መሆኑን ተናግረዋል።

የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂ በበኩላቸው፥ ለኢትዮጵያ በተለይ ለሶማሌ ክልል ደረጃውን የጠበቀ የወደብ አገልግሎት እንደሚሰጡና ከወደብ የሚወርዱ እቃዎች በሰላም እንዲደረስ ይደረጋል ማለታቸውን ከሶማሌ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.