ዶ/ር ሊያ ብሄራዊ የተሀድሶ ህክምና አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በመቋቋም ሂደት ላይ ያለውን የብሄራዊ የተሀድሶ ህክምና አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ በፊት የሚኪሊላንድ የአካል ተሀድሶ አገልግሎት ማዕከል በመባል የሚጠራውን ማዕከል ይዞታ ላይ እየተደራጀ መሆኑን ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በብሄራዊ ደረጃ የተሀድሶ ህክምና የልህቀት ማዕከል እንዲሆንና የአካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ትኩረት በመስጠት የመሰረተ-ልማት ማስፋፍያና ማሻሻያዎች፣ ዘመናዊ የአጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማምረቻ ማሽኖችና የተሀድሶ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች እንዲሟላለት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታና ማደራጃ ስራዎች ሲጠናቀቁ ለተገልጋዮች ጥራቱን የጠበቀ እና ተገልጋይ ተኮር አጠቃላይ የተሃድሶ ሕክምና አገልግሎቶችን መስጠት፣ የተለያዩ የሰው ሰራሽ አካላትን እና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማምረትና ማቅረብ፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን መስጠት እና ጥናትና ምርምር ማድረግ አላማዎቹ ናቸው፡፡
የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ በቅርቡ ስራ የሚጀምር ሲሆን፤ ስራዉ በዚህ ደረጃ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!