Fana: At a Speed of Life!

የበጀት ዕቅዱ ለዋጋ ንረት ትኩረት እንዲሰጥ ኮሚቴው ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የበጀት ዕቅዱ ለዋጋ ንረት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

 

ኮሚቴው ከገንዘብ ሚኒስቴር አስረጂዎች ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ አዲሱ የበጀት ዕቅድ ለዋጋ ንረት ትኩረት እንዲሰጥ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በዛሬው ዕለት ለሚኒስቴሩ አስረጂዎች አቅርቦ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱም በአዲሱ የበጀት ዕቅድ መካተት ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በስፋት አመላክቷል፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር በአስረጅነት የመጡት የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ መኮንን፥ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የአጭር ጊዜ እና የመካከለኛ ጊዜ ተብለው የተለዩ መፍትሔዎች መታቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፍላጎትን እና አቅርቦትን ለማመጣጠን በመንግስት በኩል የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አማካሪው አስገንዝበዋል፡፡

ቀደም ሲል በተካሄዱት የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች ከዓቅም እና ከጥራት ጋር በተያያዘ ውስንነቶች መኖራቸው ስለተረጋገጠ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

የክልሎች በጀት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ባለፉት 10 ወራት ክልሎች እንደአጠቃላይ 22 ቢሊየን ብር የጋራ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመትም ለክልሎች በተገፋው በጀት 15 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ መደረጉን መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ ኮሚቴው ያነሳቸውን አስተያየቶች እንደግብዓት በመውሰድ ክፍተቶችን እንደሚሞሉ አስረድተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ አገራዊ ቢሆንም የሚገዙትን ግብዓቶች ለመግዛት ተግዳሮት እንደነበር ሚኒስቴር ዴኤታዋ አስረድተው፥ ቀጣይ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመተባበር የሚቀረፍበትን መንገድ አቅጣጫ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለመጡ አስረጅዎች ለሰጡት ማብራሪያ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.