ፍርድ ቤቱ የህወሓት ሽብር ቡድን አባላት ሕንፃዎች በገለልተኛ አስተዳዳሪ ተይዘው እንዲተዳደሩ ወሰነ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህወሓት ሽብር ቡድን አባላት ሕንፃዎች በገለልተኛ አስተዳዳሪ ተይዘው እንዲተዳደሩ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሰኔ 16፣ 17 እና 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዋና ዋና የህወሓት የሽብር ቡድን አባላት የንግድና የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ ገለልተኛ አስተዳዳሪ እንዲሾም ውሳኔ ሰጥቷል።
በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት ÷ ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ የሰጠው የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የወንጀል ምርመራ እና የሃብት ጥናት እየተከናወነ መሆኑን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
በዚህም ቡድኑ ከሕንፃዎቹ የሚያገኘውን ገቢ የሽብር ተግባሩን ፋይናንስ ለማድረግ እንዳያውል ለመከላከል፣ በተጠረጠሩበት የሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሀብታቸው የሚወረስ በመሆኑ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የሽብር ቡድኑ በመከላከያ የሰሜን ዕዝ ሀብት፣ በተለያዩ መሠረተ ልማቶች እና ስቪል ተቋማት ላይ ላደረሰው ውድመት እና ጉዳት ለማካካሻነት የሚውል በመሆኑ እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን ንብረት የያዙ አካላት የሚፈጽሙትን ምዝበራ ለመከላከል ሲባል በተጠረጠሩበት እና በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ገለልተኛ አካል እንዲያስተዳድራቸው ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ሕንፃዎችን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚገኘው ኮመርሺያል ኖሚኒስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እንዲያስተዳድር ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህ ውሳኔ አስተዳዳሪ የተሾመላቸው የንግድ እና መኖሪያ ሕንፃዎች አጠቃላይ ብዛት ከ30 በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከልም፡-
በ ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ስም አዲስ አበባ የሚገኙ 2 (ሁለት ሕንፃዎች)፣
በ ጄ/ል አበበ ተክለሃይኖት ስም አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ G+5 ሕንፃ (ወለላ ሕንፃ)፣
በ ብ/ጄ ምግበ ሃያለ ስም አዲስ አበባ እና መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንፃዎች፣
በ ብ/ጄ ታደሰ ወረደ ስም መቀሌ የሚገኙ 2 (ሁለት) ሕንፃዎች፣
በ ብ/ጄ ተክላይ አሸብር ስም አዲስ አበባ የሚገኝ G+5 ሕንፃ (ብሌን ሕንፃ)
በ ብ/ጄ ዮሀንስ ወ/ጅወርጊስ ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) ሕንፃዎች፣
በ ሜ/ጄ ሕንፃ ወ/ጊወርጊስ ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንፃ፣
በ ሜ/ጄነራል ኢብራሂም አብዱል ጄሊል ስም መቀሌ የሚገኝ 1 (አንድ) ሕንፃ እና
በ ሃይለ ተስፋኪሮስ ገ/ሕይወት ስም መቀሌ የሚገኙ 3 (ሦስት) የነዳጅ ማደያዎች
ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በዶክተር አዲስ አለም ባሌሜና የሜጀር ጀኔራል ጻድቃን ባለቤት ወይዘሮ ኤልሳ አሰፋ ተክለሚካኤል ስም የሚገኙ ሕንፃዎችን ጨምሮ በሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ሃብት ላይ አስተዳዳሪ ለማሾም እየተሰራ መሆኑን ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላትን ንብረት በኪራይ፣ በውክልና፣ በጠባቂነት፣ በአደራና በሌላ ማናቸውም መንገድ ይዘው የሚገኙ አካላት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሃብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ቢሮ በአካል በመቅረብ ወይም በስልክ ቁጥር 0112733154 ወይም በEmail፡- assetrecovery@eag.gov.et በማሳወቅ ራሳቸውን ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!