Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ እስካሁን የ221 ምርጫ ክልልች ውጤት መሰብሰቡን አስታወቀ

አዲስ አባበ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከተከናወነባቸው 440 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች እስካሁን የ221 ውጤት መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ አንድ የምርጫ ጣቢያ ውጤት በአምስት ቀናት ውስጥ ወደ ምርጫ ክልል መቅረብ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

በዚህም ቀሪዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውጤት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

እስካሁን ባለው ዝቅተኛው የምርጫ ክልል ውጤት ያሳወቀው የአማራ ክልል ሲሆን ከ125 የምርጫ ክልሎች 44ቱን አሳውቋል፤ በአንጻሩ ኦሮሚያ ክልል 125 የምርጫ ክልል ውጤቶችን አሳውቋል ነው ያሉት፡፡

ድምፅ እንደገና በመቁጠር እያረጋገጡ ያሉ የምርጫ ክልሎች መኖራቸው ለውጤቱ መዘግየት ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም እስካሁን 10 የምርጫ ክልሎች ብቻ ውጤት ማሳወቃቸው ነው በመግለጫው የተመላከተው፡፡

ቦርዱ እንደገለፀው የምርጫ ክልሎቹ የነገውን ቀን በሚገባ በመጠቀም ሁሉም የምርጫ ክልሎች ሰኞ ውጤታቸውን ለቦርዱ ማሳወቅ አለባቸው፡፡

እስካሁን እስከ ስምንት የሚደርሱ የምርጫ ክልሎች ውጤታቸውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አድርሰው የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘታቸውንም አንስተዋል፡፡

የጋምቤላ እና ሲዳማ ክልሎች ግን ከነበረው የድምፅ አሰጣጥ መዘግየት ጋር በተያያዘ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደማይካተቱ ቦርዱ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የምርጫ ክልሎች ውጤት በ10 ቀናት እንዲሁም ጠቅላላ የምርጫው ውጤት በ20 ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋልም ነው ያሉት አማካሪዋ፡፡

በሌላ በኩል ቦርዱ ዘግይቶ ደረሰኝ ባለው መረጃ በድሬዳዋ 6 የምርጫ ጣቢያዎች በነበረ የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ምክንያት ለክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዳልተካሄደባቸው ተገልጿል፡፡

እነዚህ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባም በተገቢው ያልተከናወነባቸው እንደነበሩ በማንሳት በቀጣይ የሚወሰነው አስተዳደራዊ ውሳኔ በቦርዱ የሚገለፅ ይሆናል ተብሏል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታን በተመለከተ ሁሉም ፓርቲዎች በተወዳደሩበት ጣቢያ በወረቀት የተጠቃለለ ቅሬታ በማስረጃ እንዲያስገቡ መጠየቁን ያስታወሰው ቦርዱ፥ እስካሁን ባለው ሂደት ግን የፓርቲዎች አቤቱታ ተቆራርጦ እንደመጣለት አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የአቤቱታ ጊዜው በነገው ዕለት የሚጠናቀቅ ይሆናልም ብሏል ቦርዱ፡፡

በምርጫው ሂደት በተለይም በደቡብ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ጠቅለል ያለ “የምርጫ ይደገም” ጥያቄ ያበቀቡ ፓርቲዎች መኖራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ ከህግ ድንጋጌ ጥሰት አኳያ ባሉ አካሄዶች ደረጃ የተፈጠረ ወሳኝ ችግር የሌለ በመሆኑ ፓርቲዎች ላቀረቡት አቤቱታ ብቻ በሁለት ቀናት ውስጥ አስተዳደራዊ እርምጃ እወስዳለሁም ብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ቦርዱ በወሰነው ወሳኔ መሰረት በደቡብ ክልል ቁጫ ምርጫ ክልል ሲደርሱ የነበሩ የመደበኛነት ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የድምፅ ቆጠራ እና ማዳመር ስራው እንዲቆም ተደርጓል፡፡

በሶዶ ለማ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.