Fana: At a Speed of Life!

የህውሃት የጁንታ ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሸባሪው የህውሃት ጁንታ ቡድን ርዝራዦች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ላይ የፈፀሙትን ጥቃት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በትግራይ ክልል በሚገኘው አቢ አዲ በተባለ አካባቢ የአሸባሪው የህውሃት ጁንታ ቡድን ርዝራዦች ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ሰራተኛ በሆኑ ረዳት አስተባባሪ ዮሃንስ ሃለፎም እና የመኪናው አሽከርካሪ ቴዎድሮስ ገብረማርያም በተባሉ ኢትዮጵያውያን እና ማሪያ ሄርናንዴዝ በተባለች ስፔናዊት አስተዛባሪ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ላይ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በፈፀሙት ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ኮሚሽኑ የተሰማውን ጥልት ሀዘን እየገለፀ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ይመኛል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሟሚ ለጋሽና አርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ለሰራተኞቹ ደህንነት ሲባል ማንኛውም እንቅስቃሴ በመከላከያና በፀጥታ አካላት እጀባ መካሄድ እንዳለበት ያስታወቀ ቢሆንም አልፎ አልፎ የተወሰኑ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ያለአጃቢ በተናጠል በመንቀሳቀሳቸው ለመሰል የሽብር ቡድኑ ጥቃቶች እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡

የዓለም ማህበረሰብም ይህንንና ለሎችም የሽብርተኛው የህውሃት ጁንታ ቡድን ርዝራዦች የተለመዱ በሰው ልጅ ላይ የፈፀሟቸው ግድያዎች ኢሰብአዊ፣ አሰቃቂና አስነዋሪ ድርጊቶችን በሚገባ ተገንዝቦ ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ለደህንነታቸው ሲባል ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እያስገነዘበ በአካባቢው ሽብርተኛውን የህውሃት የጁንታ ቡድን ርዝራዦችን አድኖ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.