የሀገር ውስጥ ዜና

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ44 ሚሊየን ዶላር በላይ  የውጭ ምንዛሪ ገቢ አመነጨ

By Meseret Demissu

June 28, 2021

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ44 ሚሊየን ዶላር በላይ  የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማመንጨቱን የፓርኩ  ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

በዚህም በፓርኩ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ በተያዘው በጀት አመት 44 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደተቻለ  ስራ  አስኪያጇ  ትንሳኤ ይማም ገልጸዋል።

የፓርኩ የስራ እንቅስቃሴ በዛሬው እለት ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት በተውጣጡ ጋዜጠኞች እየተጎበኘ ነው።

በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶች በዋናነት በጨርቃ  ጨርቃ ምርት ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

ፓርኩ በሁለት ምዕራፍ የተገነባ ሲሆን÷ በአጠቃላይ በ353 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እና በውስጡም ብዙ  ፋብሪካዎችን የያዘና ሙሉ በሙሉ የተሟላ መሰረታዊ የኢንዱስትሪ ፓርክ አገልግሎቶች የተሟሉለት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ፓርኩ በአሁኑ ወቅት ከ18 ሺህ 900 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን  17ሺህ የሚሆኑት ሠራተኞች ቋሚ ቅጥር የፈፀሙ ናቸው ብለዋል።

አያይዘውም ፓርኩ የስራ ዕድል ለመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እና የቴክኖሎጂ ልምድ የመውረስ ዓላማን ይዞ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ሠራተኞች የሚገጥማቸውን ጫና ለመቀነስ ሲባልም በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ድርጅቶችን በማስተባበር በግቢው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደተጀመረ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!