Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የምርጫው ሂደት ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ መጠናቀቁን የክልሉ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በአፋር ክልል ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ በምርጫው ዙሪያ በሰመራ ከተማ ያደረገውን ውይይት ሲያጠቃልል የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ምክትል ሊቀመንበርና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሀሰን ዳውድ ሀሰን በሰጡት መግለጫ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የውጭና የውስጥ ጸረ-ሠላም ሃይሎች ምርጫውን ለማደናቀፍና ሀገሪቱን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ከሰሩት ስራ አኳያ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ እንደ ሀገርና ህዝብ ትልቅ ድል ነው ብለዋል።

በምርጫው ህዝቡ ያሳየው ንቁ ተሳትፎ መቼም ቢሆን በሀገሩ ሉአላዊነት፣ አንድነቱንና ሰላሙ ዙሪያ እንደማይደራደር በማያሻማ ቋንቋ ለአለም ህዝብ ያሳየበት መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም ህብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎችና የጸጥታ መዋቅሩ የተጫወቱት ሚና የማይተካ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በሂደቱ የማስፈጸም ተቋማዊ አቅም ውስንነትና ተያያዥ ተግዳሮቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እንደሚገመት ገልጸው፤ “ይህም ዴሞክራሲ በሂደት የሚመጣ በመሆኑ እየተለማመድን ተግዳሮቶችን ደረጃ በደረጃ እየፈታን የሚገነባ ነው”ብለዋል።

ለዚህም የጋራ ምክር ቤቱ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቀድሞዎቹ በተሻለ አሳታፊ፣ ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደን በበኩላቸው ፓርቲያቸው ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የተጣለበትን ሃላፊነቱ ለመወጣት ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ያጋጠሙ ጥቃቅን ችግሮች በጋራ ውይይት እየፈቱ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.