Fana: At a Speed of Life!

ተመራጩ መንግስት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል- ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ተመራጩ መንግስት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የምጣኔ ሃብትና አለምአቀፍ የህግ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብትና ልማት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ንጉሴ ስሜ አሁን ላይ እንደ ሃገር የሚስተዋለዉን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በዋናነት የምርት ውስንነትን በመሰሉ አንኳር የችግሩ መንስኤዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል ፡፡
ገንዘብ በብዛት ወደ ገበያዉ መሰራጨት ፣ ፍላጎት ከፍ ባለደረጃ መጨመር፣ የግብአት ውስንነቶችና ተያያዥ ችግሮች ለሸቀጦች የዋጋ ንረትና የኑሮ ዉድነት አባባሽ ምክንያት ሆነዉ እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡
ኢንቨስትመንትን ማበረታታትና የመሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚገባ ያስረዱት የምጣኔ ሃብትና የልማት ተመራማሪዉ በቀጣይ ህዝባዊ ቅቡልነቱ ታዉቆ ወደ ስራ የሚገባዉ መንግስት በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ በቂ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ገልፀዋል ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ የህግ መምህርና ተመራማሪ አቶ ደጀኔ የማነ በበኩላቸው÷ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ጉዳይ ለነገ የሚተዉ የቤት ስራ እንዳልሆነ አስረድተዋል ፡፡
ፍትህ በግለሰቦች እጅ እንዳትወድቅም ተመራጩ መንግስት ትኩረት ስጥቶ ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ደጀኔ ፍትህን ለማስፈን አቅም ያላቸውን ተቋማት መገንባት እንደሚስፈልግ ይናገራሉ ፡፡
ሃገራዊ ሰላምና መረጋጋት ከምጣኔ ሃብት ግንባታዉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለዉ መሆኑን ያነሱት ምሁራኑ በህዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን የሚመጣዉ መንግስት ወይም የፖለቲካ ፓርቲ የዜጎችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች መፍታት ቀዳሚ ስራዉ ሊሆን ይገባልም ነዉ ያሉት ፡፡
በአወል አበራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.