የሀገር ውስጥ ዜና

ከአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች በጉለሌ እዕዋት ማዕከል ችግኝ ተከሉ

By Tibebu Kebede

June 30, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች በጉለሌ እዕዋት ማዕከል ችግኝ ተከሉ።

በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ከአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሁሉም ቤተእምነቶች ከተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ችግኝ ተክለዋል።

የሀይማኖት ተቋማት ምዕመናን በማስተባበር ለችግኝ መትከያ በተዘጋጀላቸው ሰፍራ እና በየእምነት ተቋሞቻቸው ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ለመጪው ትውልድ ልምላሜን ለማውረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል።

እምነትን ከማራመድ ውጪ በልማት በተለይ በማህበራዊ አገልግሎት እና በአካባቢን ልማት እና በሌሎች ተግባራት እያበረከቱት ያለውን ተሳትፎ በይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፈጣሪ ምድርን ሲፈጥር አረንጓዴ አድርጎ ፈጥሯል፤ሰውም አካባቢውን በመጠበቅ ለኑሮ የተመቸ እንድትሆን እና ወደ ቀድሞ አረንጓዴያማነት ለመመለስ በቤተ እምነቶች አካባቢ ችግኞችን በመትከል እና የተተከሉትን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምድርን አረንጓዴ ስናለብስ በህዝብ መካከል መስተጋብርን እና መተሳሰብን እንፈጥራለን ያሉት የሀይማኖት አባቶች ቤተ እምነቶች ሰፊውን ድርሻ በመውሰድ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል ስራ የተጀመረ ሲሆን÷በአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነትም ከ1ሚሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!