Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያወጀችው የተኩስ አቁም የሚበረታታ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀገራ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔ ጥሩ እርምጃ መሆኑን ገለጹ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የተኩስ አቁም መልካም እርምጃ መሆኑን አስታውቋል፡፡

እርምጃው በክልሉ የሚስተዋለውን ግጭት ማስቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲሰራጭ ካስቻለ አበረታች ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በመግለጫው አመላክቷል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በበኩሏ÷ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደምትደግፍ ገልጻለች።

ውሳኔው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ቻይና እና ብሪታኒያም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የደረሰችው የተኩስ አቁም ውሳኔ ትክክለኛ እና የሚበረታታ እርምጃ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ጉዳዩን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ የተደረሰው የተኩስ አቁም የሰብዓዊ እርዳታን ለተጎጂዎች በተገቢው ሰዓት ለማድረስ እና ችግሩን ለመፍታት ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው የተኩስ አቁም መልካም እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.