Fana: At a Speed of Life!

ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ለሚቀርቡላቸው ችግኞች ለተከላ የሚመች የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠዋል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ለሚቀርቡላቸው ችግኞች ጎረቤት ሀገራት ለተከላ የሚመች የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጣቸውን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ገለጸ።
ሩዋንዳና ኡጋንዳም ኢትዮጵያ የችግኝ ድጋፍ እንድታደርግላቸው ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነት ከሦስት ዓመት በፊት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን መጀመሯ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶሰት ዓመታት የተጠናከረ የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
ዘንድሮም ‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ›› በሚል መሪ ሃሳብ ብሄራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተጀመረ ሲሆን 6 ቢሊየን ቸግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
ለጎረቤት ሃገራት ደግሞ 1 ቢሊየን ችግኞችን ለማድረስ የታሰበ ሲሆን ሀገራቱ ችግኞቹን ተቀብለው ለመትከል አመቺ ወቅት እየጠበቁ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ዓለምን እየፈተነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ሃገራት በተናጠል በሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሊገታ ስለማይችል የትብብር ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ታዳጊ ሃገራት ምንም እንኳን ለአየር ንብረት መዛባት ያላቸው ሚና ዝቅተኛ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች በመሆናቸው ለዘርፉ ልማት ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለደቡብ ሱዳን 91 ሚሊየን፣ ለሱዳን 356 ሚሊየን፣ ለኤርትራ 29 ሚሊየን፣ ለጂቡቲ 9 ሚሊየን፣ ለሶማሊያ 129 ሚሊየን እንዲሁም ለኬኒያ 380 ሚሊየን ችግኞችን ለማድረስ ተዘጋጅታለች።
የችግኝ ድጋፉ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ አገሮች በተጨማሪ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ባሳዩት ፍላጎት መሠረት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም. በተከናወነ ሳይንሳዊ የሳተላይት ቆጠራ በ2007 ዓ. ም. በ15 ነጥብ 5 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ብሏል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመላ ኢትዮጵያ የተለያየ ዝርያ ያላቸው 9 ቢሊየን አገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.