Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ሃገር ታዛቢዎች ነፃ ሆነው እንዲታዘቡ መደረጉ በምርጫው የታየ መልካም አጋጣሚ ነበር-ኢሰመጉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተካሄደው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ የውጭ ሃገር ታዛቢዎች ነፃ ሆነው እንዲታዘቡ መደረጉ በምርጫው የታየ መልካም አጋጣሚ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታወቀ።
ኢሰመጉ በቅድመ ምርጫ በድምፅ መስጫ ዕለትና ድህረ ምርጫ ወቅቶች ያለውን አጠቃላይ ሂደት የታዘበውን አስመልክቶ ቅድመ መግለጫ ሰጥቷል።
ምርጫው በተከናወነባቸው በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የጎላ የፀጥታ ችግር አለማጋጠሙን የገለጸው ኢሰመጉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለሚፈጠሩ ችግሮች ምላሽ የሰጠበት ፍጥነት እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገር ታዛቢዎች ነፃ ሆነው እንዲታዘቡ መደረጉ በምርጫው የታዩ መልካም አጋጣሚዎች እንደነበሩ በመግለጫው ተገልጿል።
ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች አለመዘጋጀቱ፣ በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚደረገው የምርጫ ገለፃና ማብራሪያ ወጥነት የሌለው እንደነበር፣ የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ባጋጠመባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ምርጫ ቦርድ እውቅና የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ መደረጉ የሚሉት በምርጫው ወቅት ከነበሩ ችግሮች መካከል ይገኙበታል ብሏል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ይህ ቀዳሚ መግለጫ የተዘጋጅው በሁለቱ የድምፅ መስጫ ቀናት በተሰበሰቡ መረጃዎች ብቻ በመሆኑ በቀጣይ ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ ሊለወጡ የሚችሉ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.