Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታው ምክር ቤት መንግስት በትግራይ ያደረገውን የተናጥል የተኩስ አቁም አደነቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያደረገውን የተናጥል የተኩስ አቁም አደነቀ፡፡

ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን፥ በስብሰባው ወቅትም በመንግስት የተወሰደውን የተኩስ አቁም በማድነቅ እርምጃው በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል፡፡

ዘላቂ ሰላም ከማምጣት አንጻርም ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ሃገር አቀፍ ውይይት ሊደረግ ይገባልም ነው ያለው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍና እንዲያበረታታም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር ተያይዞም ረጂ ድርጅቶች በክልሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያሳድጉም ነው ምክር ቤቱ የጠየቀው፡፡

ከዚህ ባለፈም የተከዜ ድልድይ መፍረሱን ተከትሎ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ የአውሮፕላን በረራ መፍቀዱንም አድንቋል፡፡

በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያለ ስራዎች ሊበረታቱ እና እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አያይዘውም የተኩስ አቁሙ በክልሉ የሚደረገውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማሳደግ እንዲረዳ ታስቦ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉን ያሳተፈ ውይይት ለማድረግ እድል እንደሚሰጥም አስረድተረዋል፡፡

ከሰብአዊ ድጋፍ አንጻርም መንግስት ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ በንግግራቸው በኢትዮጵያ ላይ አላግባብ እየተደረጉ ያሉና የሚደረጉ ጫናዎች ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የተወሰኑ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራትም የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን አቋም በማድነቅ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሩሲያ ኢትዮጵያ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሳ ለመገንባት ያደረገችውን ጥረት አድንቃለች፡፡

የትግራይ ክልል ጉዳይም የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ነው ብላ እንደምታምን እና የፀጥታው ምክር ቤትም እርግጠኛ ያልሆኑ እና ሃሰተኛ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ ችግሮችን ከማባባስ እንዲታቀብም ጠይቃለች፡፡

በተመድ የሩሲያ ተወካይ አምባሳደር ነቤንዚያ የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዜጎች እና የአፍሪካ ሀገራት የመንግስትን እርምጃዎች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቻይና በበኩሏ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር እንዳለበት ገልጻለች፡፡

በተመድ የቻይና ተወካይ አምባሳደር ዳኢ ቢንግ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ለመፍታት ቻይና የአፍሪካ ህብረት ሚናን እንደምትደግፍ ተናግረዋል፡፡

መንግስት የወሰደው እርምጃ ለትግራይ ክልል መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስም፥ ምክር ቤቱ አቋሙን እንዲያስተካክል አሳስበዋል፡፡

ኬኒያ በበኩሏ የመንግስትን እርምጃ በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን አረጋግጣለች፡፡

በመንግስት የተወሰደውን የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ ገልጻ በትግራይ የታጠቁ አካላትም የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቃለች፡፡

ሀገራትም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪዋን አቅርባለች፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.