Fana: At a Speed of Life!

አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማስተሳሰር የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረትን መከላከል ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረት ለመከላከል የአመራሩን ሚና በማሳደግ የህብረት ስራ ማህበራት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በምክክሩ የአምራች ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ቀጥተኛ የግብይት ትስስሮሽን አጠናክሮ ማስቀጠል ምክንያት የለሽ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሚናው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የዋጋ ንረት ላይ መምከር እና መፍትሄ ማስቀመጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅድመ ምርጫ ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመፍጠር የተሄደበትን ተግባር ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዋጋ ንረቱ እንዲስተካከል በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የአምራቹን እና የህብረት ስራ ማህበራትን የግንኙነት መስመር በማሳጠር የሸማቹን ችግር መፍታት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

በአምራቹና በህብረት ስራ ማህበራት መካከል ያለውን ሰንሰለት ማሳጠር እና ሸማቹ ላይ የሚደርስበትን መንገድ ማቅለል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ብዙ ዋጋዎች አዲስ አበባ ላይ የሚወሰኑ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ፥ ይህ እንደሃገር የዋጋ ንረትን ሊያባብስ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በተለይም አዲስ አበባ ላይ ያለው አመራር ችግሩን ከስሩ ለመፍታት የቀዳሚነቱን ሚና ሊወስድ ይገባልም ብለዋል፡፡

ይህን ማድረግ ከተቻለ እንደሃገር ሊከሰት የሚችለውን ያልተገባ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻልም አውስተዋል፡፡

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው ምክንያት አልባ የዋጋ ንረት እንደሚስተዋል ጠቁመው፥ ይህን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የህብረት ስራ ማህበራት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡

የህብረተሰቡን በተለይም የመካከለኛ እና ዝቅተኛውን ማህብረሰብ የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት ህብረት ስራ ማህበራት እንዲጎለብቱ አመራሮች ጠጋ ብለው ሊያግዟቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.