Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል-ወ/ሮ ሙፈሪሃት

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።

የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የከፍተኛ አመራር አባላት የውይይት መድረክ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ በመንግስት አገልግሎት ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች እርካታ መፍጠር እንደ አገር ለተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት አስተዋጽኦ አለው።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች በጥናት መለየታቸውን ጠቁመው፤ ከተለዩት ጉዳዮች መካከል የአገረ መንግስትና የብሔረ መንግስት ግንባታ አለመጠናቀቅ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ሁለት አንኳር ጉዳዮች ለዘላቂ ሰላም መሳካት ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

የአገረ መንግስት ግንባታን ለማጠናቀቅ ጠንካራ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ “ከግለሰብ ጀምሮ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና በተቋም ደረጃ የሚረጋገጥ ሰላም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ብቃት ያለው፣ አገልጋይ፣ በእውቀትና ክህሎቱ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሰ የሰው ሀይል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ይህም የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ምላሽ ሰጪነት አቅም እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

የተቋማትን አሰራር በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ ማዘመንና ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች ክብር ያለው አገልግሎት መስጠታቸውን ማረጋገጥ መቻል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ይህም በዜጎችና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመን የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ ለተጀመረው የዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የራሱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሲቪል ሰርሺስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው ሰላምና የመንግስት አገልግሎት ቁርኝታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት አገልግሎት ዘርፎች ሁሉ ቅድሚያ ለዜጎች ክብር ምላሽ ሊሰጥ በሚችል አደረጃጀት በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

“አገልግሎት በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በሙያ ብቃት የሚሰጥ ከሆነ ዜጎች የአገልግሎት እርካታ ስለሚያገኙ ሰላማቸውን በባለቤትነት ይጠብቃሉ” ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.