የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለመንግስት ምስጋና አቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መንግስት ‘ለ60 ዓመታት ገደማ’ ያቀረበውን ጥያቄ ለመመለስ ውሳኔ በማስተላለፉ መደሰቱን በመግለጽ ምስጋና አቅርቧል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 78ኛ መደበኛ ስብሰባው በስድስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
ውሳኔ ካሳለፈባቸው አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት እንዲሰጠው የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነበር።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሲቀርብ ነበር።
ለዓመታት ሲንከባለል የቆየውና የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ የነበረውን በአሁኑ ወቅት መንግስት ለመመለስ ያሳለፈውን ውሳኔም አድንቀዋል።
እንዲሁም የሙስሊም ባንክ እንዲቋቋም ከመፍቀድ ጀምሮ በርካታ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ባለው መንግስት አማካኝነት ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ህዝበ ሙስሊሙን ያስደሰተው ጉዳይ ህዝበ ክርስቲኑንም የሚያስደስት እንደሚሆን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ረቂቅ አዋጁ በአፋጣኝ ጸድቆ ጥቅም ላይ ይውል ዘንድም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትኩረት እንዲሰጠው መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።