Fana: At a Speed of Life!

ዘንድሮ በዓባይ ተፋሰስ ከ4ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ይተከላል – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በዘንድሮው ክረምት በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ከ4ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ የጥምር ደን ችግኝ የሚተከል መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በአግባቡ በማከናወን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል በመከላከል የአገልግሎት ዕድሜውን ለማስረዘም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ወሳኝ እንደሆነ ተነግሯል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ እንደገለጹት፥ ለዘንድሮ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ከ7 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ እየተተከለ ነው።

በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ብቻ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ እንደሚተከልም ገልጸዋል።

በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር የህዳሴ ግድቡን ከደለል ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ተፋሰሱ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎችን እንደሚሸፍን የገለጹት አቶ ሳኒ፥ “በእነዚህ አብዛኛው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ ተጀምሯል” ብለዋል።

የግድቡን ውሃ የመያዝ አቅም የሚጎዱ ሁኔታዎችን መከላከል እንደሚገባ ገልጸው፥ የግድቡን ህልውና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

አባይን አልምቶ ለመጠቀም በዲፕሎማሲው መስክ እየተደረገ ያለው ትግል የግድቡን ህልውና በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድም መደገም እንዳለበት ገልጸዋል።

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው፥ የህዳሴ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉሩና ለዓለም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በተለይ የውሃ ሃብትን ለማሳደግ፣ ለሃይል ማመንጫ፣ ለብዝሃ ህይወት ጥበቃና ለደን ልማት እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የአረንጓዴ ልማቱ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና ለአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.