በሀረር ከተማ በጥምቀት በዓል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረር ከተማ በጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ የሰለምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ዩያ በሰጡት መግለጫ፥ ባሳለፍነው ሳምንት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል።
ሁኔታው ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት የፈጠሩት የፀጥታ ችግር ነው ብለዋል።
በተፈጠረው ችግር የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና 7 ሰዎች መቁሰላቸውን ከሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ በተጨማሪም በ11 ህንፃዎች ላይ መስታወት እና የተለያዩ ቁሳቁሶች የመሰባበር እንዲሁም ሁለት ህንፃዎች፣ ሁለት ተሽከርካሪዎችና አራት ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውንም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ባደረገው እንቅስቃሴ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከእነዚህ መካከል 63 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።
አያይዘውም የተፈጠረው ችግር የክልሉን ህዝብ በሰላም፣ በመቻቻልና በአንድነት አብሮ የመኖር እሴቱን ለመሸርሸር ያለመ የጥፋት አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ችግሩ ከሐይማኖት እና ከብሔር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውምም ነው ያሉት ኃላፊው።
በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ያነሱት ሃላፊው፥ በክልሉ ከሚገኙ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት የክልሉን ሰላም የማስጠበቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።