በባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የሮኬት ጥቃት ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢራቅ መዲና ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙ ተሰማ።
ሶስት የሮኬት ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፥ አንደኛው ሮኬት ብቻ በኤምባሲው ካፌ ላይ ማረፉ ተነግሯል።
ሌሎች ሁለት ሮኬቶች ግን በኤምባሲው አቅራቢያ ወድቀዋል ነው የተባለው።
በጥቃቱ ሶስት ሰዎች ሲቆስሉ፥ ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
አሜሪካ ግን በኢራን የሚደገፍ ወታደራዊ አንጃ ጥቃቱን ፈጽሟል ብላለች።
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አዴል አብዱል መሐዲ ጥቃቱን አውግዘው፥ መሰል እንቅስቃሴዎች ኢራቅን የጦር አውድማ ያደርጓታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በመዲናዋ ባግዳድ አሜሪካን የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎችም ተካሂደዋል።
በኤምባሲው ላይ የተፈጸመው የአሁኑ ጥቃት ከረጅም አመታት በኋላ የመጀመሪያው መሆኑ ነው የተነገረው።
ምንጭ፦ ቢቢሲ